ቱሪዝም የህዳሴው ነፀብራቅ!

ቱሪዝም የህዳሴው ነፀብራቅ!

ከተማችን አዲስ አበባ በአለም አቀፍ ጎራ አንቱታን ካጎናፀፋት እውቅና በተጨማሪ ከ86 በላይ ብሄር ብሄረሰቦች የጋራ መኖሪያ መሆኗ ልዩ ያደርጋታል፡፡ በዚህ የተነሳም “ትንሿ ኢትዮጵያ፣ የብሄር ብሄረሰቦች ሙዝየም እና የህብር እንቁ” የሚሉ ስያሜዎችን አግኝታለች። በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በርካታ ሃገራዊ፣ አህጉራዊ እና አለም አቀፋዊ ተቀባይነቷን ተከትሎ የኮንፈረንስ ቱሪዝም ኩነት መዳረሻነት በብዙዎች ታጭታለች፡፡ የከተማ መስረተ ልማት በማስፋፋት እና አስተማማኝ ሰላም አላቸው ተብለው በቱሪስት መዳረሻነት ከሚመረጡ ዘጠኝ ከተሞች ተርታም ለመስለፍ በቅታለች፡፡
መዲናችን ባላት ታሪካዊ፣ ጥንታዊ እና ባህላዊ የቅርፅ ብሎም በርካት ቱፊት ዘመናዊ እና ቀልጣፍ አገልግት በሚሰጠው የቦሌ አለም አቀፍ አየር መንገድ ያለድርድር ቀዳሚ ምርጫ እንድትሆን አግዟታል፡፡ መሽቶ በነጋ ቁጥር አዲስ እየሆነች ያለችው ከተማ በበርካቶች አንደበት ሲመሰከርላት ማድመጥ የተለመደ ሆኗል፡፡ የአዲሱ ሚሊንየም አስረኛ አመት ምክንያት በማድረግ በከተማችን የባህልና ቱሪዝም እንቅስቃሴ አስመልክቶ ከአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ ከአቶ ገ/ፃዲቅ ሐጎስ ጋር ቆይታ አድርገናል።
ህዳሴ፡- የከተማችን የቱሪዝም ኢንዱስትሪ እድገት ባለፉት አስር አመታት ምን ይመስል እንደነበር ቢገልፁልን?
አቶ ገ/ፃዲቅ፡- የቱሪዝም ኢንዱሰትሪው እድገት ከአስር ዓመት በፊት ከነበረበት ከፍተኛ ለውጥ እያሳየ እንደሚገኝ ማረጋገጥ ይቻላል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በ2000 ዓ.ም በአዋጅ የተቋቋመ ሲሆን የባህልና ቱሪዝም መረጃዎችን ማሰባሰብ፣ ማጠናከርና ማሰራጨት እንደ አንድ ተግባር ተለይተው የተሰጡት ሃላፊነቶች በመሆናቸው በ2003 ዓ.ም በሁሉም ክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች አጠቃላይ መረጃ የማሰባሰብ ስራ አከናውኗል። በ2008 ዓ.ም ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ ስራው በተሻለ ሁኔታ ተከናውኖ ከተማችን በቱሪዝም ኢንዱስትሪው ዘርፍ የምትገኝበትን ተጨባጭ ሁኔታ ለመዳሰስ የተቻለ ሲሆን በዚህም ከተማችን ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ለውጥ ላይ እንደምትገኝ አረጋግጠናል።
ከአነስተኛ እስከ ባለ ኮኮብ ሆቴሎች፣ የምሽት ክለብና የመሰንቆ ቤቶች፣ የሆቴልና ቱሪዝም ማሰልጠኛዎችና አስጎብኚ ድርጅቶችን የመሳሰሉ የቱሪስት አገልግሎት ሰጭ ተቋማት በከፍተኛ ሁኔታ ጨምረዋል። በባህል አገልግሎት ዘርፍም በቴአትር፣ በፊልም፣ በስነ ፅሁፍ፣ በሙዚቃ፣ በስዕልና ቅርፃ ቅርፅ ላይ የተሻለ መነቃቃት አለ።
ቢሮው ባካሄደው የምዝገባ ጥናት በ2003 በጀት ዓመት በባህል ዘርፍ የተሰማሩ 2 ሺህ 707 ተቋማት የነበሩ ሲሆን 8 ሺህ 119 ተቋማት ደግሞ በቱሪዝም በድምሩ 10 ሺህ 826 ተቋማት በዘርፍ መሰማራታቸውን ያረጋገጠ ሲሆን በ2008 ዓ.ም በተካሄደው የምዝገባ ጥናት በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተው አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ 795 ተቋማትን ጨምሮ ቁጥሩ ወደ 30 ሺህ 649 መድረሱ ተረጋግጧል። ይህም በተጨባጭ የቱሪዝም ኢንዱስትሪው በከፍተኛ ለውጥ ላይ እንደሚገኝ ያሳያል።
ህዳሴ፡- በተለይ የሆቴሎች መስፋፋትና አገልግሎት አሰጣጥ ለዘርፉ እያበረከተ ያለው አስተዋፅኦ ምን ይምስላል?
አቶ ገ/ፃዲቅ፡- በመንግስት በኩል ባለሀብቱን የሚያበረታቱ የህግ ማዕቀፎች በመውጣታቸው በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ በርካታ ባለሀብቶች በሆቴል ኢንዱስትሪው ተሰማርተዋል። በመጀመሪያው ጥናታችን በከተማችን ከነበሩት 712 ሆቴሎች 58 ብቻ ነበሩ ባለ ኮኮብ። በ2008 ባደረግነው ጥናት ግን የሆቴሎች ቁጥር 1 ሺህ 129 ከመድረሱም በላይ ደረጃቸውን የጠበቁ ባለኮኮብ ሆቴሎች 111 ደርሰዋል። የሆቴሎቹ ሙያዊ እውቀት ያለው የሰለጠነ የሰው ሀይል የመጠቀሙ ልምድና ፍላጎትም እየተሻሻለ መጥቶ ከ60 በመቶ በላይ ደርሷል። ስለዚህ ባለሀብቱ ከሆቴል ግንባታ ባለፈ የሰለጠነ የሰው ሀይል በመጠቀም አገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመን የሚያደርገው ጥረት በአስተሳሰብ ደረጃም በተግባራዊ ለውጥም መሻሻል የሚታይበት ነው። የሆቴሎች አገልግሎት አሰጣጥ በመሻሻሉ አማካኝ የቱሪስቶች የቆይታ ጊዜም እየጨመረ ይገኛል። በዚሀም ለከተማችን እድገትና የገፅታ ግንባታ የድርሻቸውን እያበረከቱ መሆኑን መጥቀስ ይቻላል።
ህዳሴ፡- ለዘርፉ እድገት የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት ምን ምን ናቸው?
አቶ ገ/ፃዲቅ፡- ለቱሪዝም እድገትና መሻሻል እንዲሁም መነቃቃት ዋነኛው ምክንያት በቢሮው ብቻ የተሰሩ ስራዎች ናቸው ብሎ መውሰድ አይቻልም። ቢሮው ከተሰጠው ተልዕኮ አንፃር የሚሰራው ስራ እንደተጠበቀ ሆኖ ነገር ግን እንደሀገር የምንከተለው የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግስት አቅጣጫ በሁሉም ዘርፍ በፈጠረው ምቹ ሁኔታ ለቱሪዝም ኢንዱስትሪውም እድገት ዋነኛ ምክንያት ነው።
ቱሪስት ወደሀገራችን በሚገባበት ጊዜ የተሻለ መንገድና የመብራት አቅርቦት የመሳሰሉትን መሰረት ልማቶች ይፈልጋል። መንግስት በሚከተለው ትክክለኛ ፖሊሲና አቅጣጫ መሰረት እንደ ከተማም እንደሀገርም የመጡ ሁሉን አቀፍ ለውጦች ለዘርፉ እድገት የማይተካ ሚና ተጫውተዋል።
ቢሮውም ከተልዕኮው አኳያ ያከናወናቸው በርካታ ተግባራት አሉ። በአንድ በኩል ከተማችንን በውስጥም በውጭም ለማስተዋወቅ በርካታ ስራዎች እያከናወንን ነው። ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይም ጭምር በቋሚነት እየተገኘን ተሞክሯችንን እናስተላልፋለን የሌሎችን ተሞክሮም በመቅሰም ተግባራዊ እያደረግን እንገኛለን። ለምሳሌ (Interactional Conference Convention Association /ICCA/) ከሚባል ከ90 በላይ የዓለም ሀገሮች የሚሳተፉበትና በቱሪዝም ዙሪያ ከሚሰራ ማህበር ጋር በየዓመቱ በቋሚ ግንኙነት በተለያዩ ጊዜ በመገኘት የልምድ ልውውጥ እናደርጋለን።
የሰው እንቅስቃሴ በሚበዛባቸው 17 ቦታዎች በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተከልናቸው የቱሪስት ካርታዎችም ከዚሁ ተሞክሮ ከተገኙት ውስጥ የሚጠቀሱ ሲሆን ቱሪስቱ በቀላሉ መጎብኘት የሚችላቸውን ቦታዎች እንዲረዳ ያደርገዋል።
በከተማችን አጭር ቆይታ የሚያደርጉ ቱሪስቶች ደግሞ አንድ ቦታ ላይ ስለከተማዋ በምስል የተደገፈ በቂ መረጃ እንዲኖራቸው የሚያስችል የአዲስ አበባ ከተማ Virtual tour የሚባል ዘመናዊና የተደራጀ መረጃ አገልግሎትም የተጀመረ ሲሆን እንዲስፋፋ ይደረጋል።
ቱሪስቱ በራሱ ቋንቋ በቂ መረጃ እንዲያገኝም ወደ ሀገራችን የሚመጡ ጎብኝዎችን ቁጥር ታሳቢ በማድረግ በእንግሊዘኛ፣ በጀርመንኛ፣ በአረብኛ፣ በፈረንሳይኛ ቋንቋዎችም ጭምር የተለያዩ ዶክመንተሪዎችን በማዘጋጀት በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በኩል ለኤምባሲዎች እንዲደርሱ እያደረግን ነው። በየደረጃው ለሚገኘው የኮሙኒኬሽን መዋቅርም በተመሳሳይ እናሰራጫለን። የተለያዩ ጋይድ ቡኮችንም እያዘጋጀን የምናሰራጭ ሲሆን ባሳለፍነው በጀት ዓመት ብቻ ከ2000 በላይ በእንግሊዘኛ ተዘጋጅቶ ተሰራጭቷል። ማህበራዊ ሚዲያዎችንም በስፋት እየተጠቀምን ወቅታዊ የከተማችንን ገፅታ እያስተዋወቅን ነው።
ሌላ ነባር የቱሪስት መዳረሻዎችንም የማልማት ስራ አከናውነናል። ለምሳሌ አራት ኪሎ ያለውን የአርበኞች ሀውልታችን ሙሉ በሙሉ ታድሶ ስራ እንዲጀምር ተደርጓል። ስድስት ኪሎ የሚገኘው የሰማዕታት ሀውልታችንም በተመሳሳይ ሙሉ በሙሉ ታድሶ ስራ ጀምሯል።
አዲስ አበባ መቶኛ ዓመቷን ስታከብር በ1979 ዓ.ም የተደራጀውና ከዛን ጊዜ ጀምሮ ምንም እድሳት ያልተደረገለት የአዲስ አበባ ሙዚየም ባለፉት ሁለት ዓመታት ውጪውም በውስጡም የያዛቸውን ቅርሶች አዲስ አበባን በሚወክል መንገድ በጥሩ ሁኔታ ተደራጅቶ ስራው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።
የቱሪስት መዳረሻዎችን የማልማትና ለቱሪስት ምቹ የማድረግ ሁኔታዎችም በቢሮው በከፍተኛ ሁኔታ እየተሰሩ ነው። የባህል ተቋማትን የማስፋት ስራም በስፋት እየተሰራ ሲሆን ለአብነትም ቴአትር ቤቶቻችን ውስን ከመሆናቸውም በተጨማሪ በአንድ ቦታ ላይ የተሰባሰቡ በመሆናቸው ደረጃቸውን የጠበቁ ተጨማሪ ቴአትር ቤቶችን ለመገንባት አቅደን እየሰራን ነው።
በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ ዘጠኝ ኤግዚቢሽን መግቢያ አካባቢ የከተማ አስተዳደሩ 350 ሚሊዮን ብር መድቦ በ5 ሺህ 400 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ እጅግ ዘመናዊ ባለ 11 ወለል ህንፃ ከሁለት ዓመት በፊት ግንባታው ተጀምሮ አሁን ላይ ከ70 በመቶ በላይ ደርሷል። ይህም ሲጠናቀቅ ለኪነ ጥበቡ ዘርፉ ትልቅ ብስራት ነው። በልደታ ክፍለ ከተማ ላይም የከተማ አስተዳደሩ በ248 ሚሊዮን ብር ተጨማሪ ሲኒማ ቤት እያስገነባ ይገኛል። በሶስት ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የሚያርፈው የራስ ቴአትር ቤት ግንባታም ቅድመ ዝግጅቱ ተጠናቋል። እንጦጦንም ሙሉ በሙሉ ለማልማት አቅደን እየሰራን ሲሆን በ4 ሺህ 200 ሄክታር ቦታ ላይ ግንባታውን ለማስጀመር ቢሮው ራሱን የቻለ ፕሮጀክት አቋቁሞ እንቅስቃሴ ጀምሯል። በአጠቃላይ ለወጣቱም ለከተማችን ነዋሪዎችም ትልቅ ብስራት የሚሆኑ በርካታ ስራዎች በከተማ አስተዳደሩና በቢሮው እየተሰሩ መሆኑን መታዘብ ይቻላል።
ህዳሴ፡- የኪነ ጥበቡ ዘርፍ ለሀገር ባህል መጎልበት የሚጠበቅበትን እየተወጣ ነው ማለት ይቻላል?
አቶ ገ/ፃዲቅ፡- ዜጎች በነፃ የመሰላቸውን የመፃፍ፣ የመግጠም፣ የመዝፈንና የመሳል መብታቸው በህገ-መንግስቱም ጭምር በመረጋገጡና ቅድመ ምርመራ በመቅረቱ ፊልሞች፣ ቴአትር እና ሙዚቃ በከፍተኛ እድገት ላይ ናቸው። ፊልሞችን ብንወስድ በብዛት የሚሰሩት ሀገርኛ ፊልሞች ናቸው አብዛኛው ተመልካችም የአገርኛ ፊልሞችን ይመርጣል። ለምሳሌ በ2009 ዓ.ም ብቻ በአዲስ አበባ በሶስቱ ሲኒማ ቤቶች (በሰኒማ አምባሳደር፣ ኢትዮጵያና አምፔር) ከ90 በላይ ሀገርኛ ፊልሞች የታዩ ሲሆን ከ103 ሺህ 800 በላይ ተመልካች ነበራቸው። በግል ሲኒማ ቤቶች ደግሞ ከዚህ ያልተናነሰ ተመልካች ፊልም መመልከቱ መገመት ይቻላል።
ፈጠራዎችም ከጊዜ ወደጊዜ እየዳበሩ እየተሻሻሉ ለቱሪዝም ኢንዱስትሪውም የበኩላቸውን ድርሻ እየተወጡ ነው። የባህል ሬስቶራንቶች ላይ ምሽት ጎራ ብትል የባህል የኪነ-ጥበብ ቡድኖችን በስፋት ታገኛለህ። እነዚህ ቤቶች ደግሞ በብዛት የውጪ ዜጎችም የሚያዘወትሯቸው ስለሆኑ ባህላችን ለማሳየት የጎላ ሚና ይጫወታሉ።
ህዳሴ፡- የመዲናችን የቱሪዝም ኮንፈረንስ እድገት በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
አቶ ገ/ፃዲቅ፡- እንደሚታወቀው ከተማችን የበርካታ ብሄር ብሄረሰቦች መናኸሪያና የበርካታ ታላላቅ አህጉራዊና አለም አቀፋዊ ተቋማት መቀመጫ ናት። በርካታ ዲፕሎማቶች የሚገኙባት በርካታ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች በየጊዜው የሚካሄዱባት በመሆኗ እነዚህን ምቹ ሁኔታዎች በመጠቀም ከተማችንን የበለጠ ለማስተዋወቅ ጥረቶች እየተደረጉ ነው።
ከተማችን ከኮንፈረንስ አቅምነቷ አንፃር ተጨማሪ ስራዎች መስራት እንዳለባቸው ታምኖበት በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ነው። ተጨማሪ የስብሰባ ማዕከላትም እየተሰሩ ነው። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንግድ ምክር ቤት ጋር በመሆን በቅርቡ በተለምዶ ሲኤምሲ ከሚባለው አካባቢ ትልቅ የኮንቬንሽን ሴንተር ለመገንባት በክቡር ፕሬዝዳንቱ የመሰረት ድንጋይ መቀመጡ ይታወሳል።
የአዲስ አበባ ኤግዚቢሽንንም ደረጃውን የጠበቀ ዓለም አቀፍ የስብሰባና የገበያ ማዕከል ለማድረገ በስፔኖች እንዲጠና ተደርጓል።
ህዳሴ፡- የከተማችን አስተማማኝ ሰላምና የህብረተሰቡ እንግዳ ተቀባይነት ለቱሪዝም እድገቱ እያበረከተ ያለው አስተዋፅኦስ እንዴት ይታያል?
አቶ ገ/ፃዲቅ፡- የቱሪስት ባህሪን ስንመለከት ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢ ሲንቀሳቀስ ቁጥር አንድ የሚያስቀምጠው መስፈርት አስተማማኝ ሰላም አለ የለም የሚለውን ነው። ከሁሉም በላይ መቅደም ያለበትም የሰላም ጉዳይ ነው። በሀገራችን አስተማማኝ ሰላም በመኖሩ በከተማችንም አስተማማኝ ሰላም በመኖሩ ነው ከተማችንን ለኮንፈረንስ ቱሪዝም፣ ለጎብኝትም ለዘመድ ጥየቃም ቱሪስቶች 24 ሰዓት ተንቀሳቅሰው በሰላም ወደመጡበት እንደሚመለሱ በመተማመን ነው የሚመጡት። ከዚህም በተጨማሪ የሀገራችንና የከተማችን ነዋሪዎች እንግዳ ተቀባይነትም የሚታወቅ ነው። ባለፉት አስር አመታት በከተማችን በርካታ ኮንፈረንሶች ተካሂደዋል። አንድም ኮሽታ ሳይሰማ እንግዶች በሰላም ገብተው በሰላም ወደሀገራቸው የተመለሱበት ሁኔታ ነው የነበረው። ለወደፊቱም እንዲህ ዓይነቱ መልካም እሴት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል። ባለፈው ዓመት ከአዲስ አበባ ውጪ በአንዳንድ የሀገራችን ክፍሎች ሰላማችንን የሚያውኩ አላስፈላጊ ሁኔታዎች በፀረ ሰላምና በፀረ ህዝብ ሀይሎች ተከስቶ ስለነበር በቱሪዝም ኢንዱስትሪው ላይ ተፅዕኖ አልንበረውም ማለት አይቻልም። በተለይም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተነሳ በኋላ ደግሞ ሙሉ በሙሉ ወደነበረበት እየተመለሰ ነው።
ቱሪስቶች በሰላም ገብተው በሰላም ሲወጡ የሀገራችንም የከተማችንም የሰላም አምባሳደሮች ይሆናሉ። ሌላ ጊዜ ተመልሰው የሚመጡበትና ሌሎችንም የሚጋብዙበት አጋጣሚ ይሰፋል። ቆይታቸውንም ያራዝማሉ። ስለዚህም የህብረተሰባችን እንግዳ ተቀባይነትና ሰላም ለቱሪዝም ኢንዱስትሪውና ለኢኮኖሚ ተጠቃሚነታችን ፋይዳው የጎላ በመሆኑ በቀጣይም መንግስትና ህዝብ እጅና ጓንት ሆነው ይሰራሉ።
ህዳሴ፡- ዓለም አቀፍ የቱሪስት ተቋማት ስለ ኢትዮጵያና ስለ አዲስ አበባ ያላቸው እይታ ምን ይመስላል?
አቶ ገ/ፃዲቅ፡- ዓለም አቀፍ የቱሪስት ተቋማት ለሀገራችንና ለከተማችን ያላቸው እይታ ለፈጣን ልማትና አስተማማኝ ሰላም ላይ የምትገኝ ሀገር በመሆኗና ከተማችንም በተመሳሳይ በፈጣን ለውጥ ላይ ስለምትገኝ በፊት ከሚያውቁት ታሪክ የተለየ መሆኑን እንደሚገነዘቡት በዓለማቀፍ መድረኮችም ጭምር የምናረጋግጠው ነው። በተጨባጭም የቱሪስት ፍሰቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ ማደጉና ከተማችን ላይ እየተደረጉ የሚገኙት በርካታ አለም አቀፍ ኮንፈረንሶች ማሳያ ናቸው። ሆኖም በቅርቡ በነበረው የፀረ ሰላም ሀይሎች ሰላምን የማወክ እንቅስቅሴ የቱሪስት ፍሰቱ ላይ የተወሰነ ተፅዕኖ እንደነበረው ታይቷል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተነሳ በኋላ ግን ከተለያዩ ሀገራት የሚገኙ የቱሪስት ተቋማት ደስተኛ ሆነው እንግዶችን እያሰባሰቡ እየላኩ ነው። በአመለካከትም በተግባርም ለውጥ መምጣቱን መረዳት ይቻላል።
ህዳሴ፡- የዘርፉ ዋና ዋና ተግዳሮቶችና የቀጣይ አቅጣጫዎች ምን ምን ናቸው?
አቶ ገ/ፃዲቅ፡- በቱሪዝም ኢንዱስትሪው ላይ ያሉት ዋና ዋና ተግዳሮቶች በእኔ እምነት ሁለት ናቸው። እስካሁን እየተሰራ ያለው እንደተጠበቀ ሆኖ አሁንም መፈታት ያለባቸው ሁለት መሰረታዊ ጉዳዮች አሉ። በአንድ በኩል የቱሪስት መዳረሻዎች ላይ በስፋት መስራት ያስፈልጋል። በሀገራችንም በከተማችንም ዋነኛ የዘርፉ ተግዳሮት ምቹ የቱሪስት መዳረሻዎች በበቂ ሁኔታ ያለመኖር ችግር ነው። ምክንያቱም ቱሪስቶች ወደ ከተማችን ሲገቡ ቆይታቸውን ማራዘም የሚችሉት የተመቸ የቱሪስት መዳረሻ ሲኖር ነው። ይህንንም በመረዳት የከተማ አስተዳደሩና ቢሮው የእንጦጦን ተራራ ሙሉ በሙሉ የቱሪስት መዳረሻ ማድረገ አለብን ብለን ለሀገር ውስጥም ለውጪም ጎብኚዎች የተመቸ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ ወደ ስራው እየገባን ነው። ሌሎች ተጨማሪ የቱሪስት መዳራሻዎችም ያስፈልጋሉ።
ሁለተኛው ተግዳሮት የሰለጠነ የሰው ሀይል እጥረት ነው። ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት በየሆቴሉ ያለውን የሰው ሀይል ከቱሪዝም ሙያ ጋር እንዲተዋወቅ ማድረግ ያስፈልጋል። ይህ ካልሆነ ቱሪስቱ ከሌላው አለም የለመደውን ፈጣንና ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት ማግኘት ስለማይችል ቆይታውን አያራዝምም ለመመለስም አይወስንም። ይህንን በመገንዘብ ቢሮው ከአዲስ አበባ ቴክኒክና ሙያ ቢሮ ጋር በመሆን ባሳለፍነው በጀት ዓመት ብቻ ከ20 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሙያተኞች የስራ ላይ ስልጠና እንዲያገኙ ተደርጓል። ባለድርሻ አካላት በተለይም የሆቴል ባለሀብቶች ህንፃውን መገንባት ሲጀምሩ የሰለጠነ የሰው ሀይሉ ላይም ጎን ለጎን በትኩረት ሊሰሩ ይገባል።
ሌሎች ሀገሮች እነዚህን ሁለት አንኳር ጉዳዮች በበቂ ሁኔታ በመመለሳቸው ከዘርፉ በከፍተኛ ሁኔታ ተጠቃሚ እየሆኑ ነው። በሌሎች ሀገሮችም የቱሪዝም ኢንዱስትሪው ዋነኛ የገቢ ምንጫቸው ነው። ይህንን ወደ ሀገራችን ለማምጣት ነው እየተንቀሳቀስን ያለው። እንጦጦን ብንወስድ በ4 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ወጪ በስድስት ዓመት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል። ከተጠናቀቀ በአስረኛ አመቱ 21 ቢሊዮን ብር እንደሚገኝበት በጥናት ተረጋግጧል። ይህም አሁን ባለው ሁኔታ የከተማችንን በጀት ግማሹን ይሸፍናል ማለት ነው። በመሆኑም የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን ትራንስፎርም ለማድረግና ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ ለማግኘት ከአስር አመት ወዲህ እንኳን በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ ነው። በቀጣይም መንግስት ህዝቡና ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው መስራት ያስፈልጋል።
ህዳሴ፡- በጣም እናመሰግናለን።
አቶ ገ/ፃዲቅ፡- እኔም በጣም አመሰግናለሁ።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*