የሥራ ዕድል ፈጠራ የከተማችን ቀዳሚ አጀንዳ!

የሥራ ዕድል ፈጠራ የከተማችን ቀዳሚ አጀንዳ!

በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄ መድረክ ላይ ከተመለከትናቸው አበይት ጉዳዮች አንዱ የህዝብ ተጠቃሚነት ነው። በቀደሙት 15 ዓመታት በኢህአዴግ አመራር ያስመዘገብናቸው የህዝብ ተጠቃሚነቶችን ብቻም አይደለም የአጤንነው። እንዲያውም መጠቀም በሚገባ ደረጃ ስፋትና መጠን ያልተጠቀመ የህብረተሰብ ክፍል ጉዳይን ይበልጥ የአተኮርንበትም ነው። በተለይም የወጣቶችና ሴቶች ተጠቃሚነት ጉዳይ ቅድሚያ ልንሰጣቸው ከሚገቡት ውስጥ ተጠቃሽ አድርገናቸዋልም።

ሁሉም የከተማ አስተዳደራችን ተቋማት እንዲሁም በርካታ አደረጃጀቶች ከመልካም አስተዳደር ስራ በተጓዳኝ ይህንኑ የወጣቶችና ሴቶችን ተጠቃሚነትና ተሳታፊነት አብይ ተግባራቸው አድርገው ይዘዋል። እነሆ ሰሞኑን ደግሞ የከተማ አስተዳደራችን የወጣቶችን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት የሚያሳድግ የንቅናቄ ፕሮግራም ይፋ አድርጓል። በዚሁ የንቅናቄ ፕሮግራምም ላይ የጉዳዩ ባለቤቶች ወጣቶች እንዲመከሩበት መድረክም ተከፍቶ ተከናውኗል። በከተማዋ 117 ወረዳዎች በተደረገው ውይይት በመንግስት እና በወጣቶች መካከል ከመቼውም በተሻለ ደረጃ መተማመን ተፈጥሯል።

ለዚህም አመላካች ከሚሆኑት ነገሮች አንዱ ለውይይት የቀረበው ሰነድ የሁሉንም የባለድርሻ አካላት ጎዶሎዎችን ነቅሶ የአወጣ መሆኑ ነው። በመንግስት በወጣቶች በኩል ከተጠቀሱ ጎዶሎዎች ባሻገር ተሳታፊዎችም ማለፊያ አድርገው ሰልቀውታል። በዚህም በዚያም የተጠቀሱ ተግዳሮቶች በእርግጥም የሚታዩና የሚጨበጡ መሆናቸው ላይ ተግባብተውበታል። ቀደም ሲል በተካሄዱ መሰል ፕሮግራሞች ሃብት የፈጠሩ፣ ከራሳቸው አልፈው ለሌሎችም የስራ እድል ምንጭ መሆን የቻሉ፣ እንዲሁም ከጥቃቅንና አነስተኛ ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪ የተሸጋገሩ ስኬታማ ወጣቶች ተሞክሯቸውን ገልፀዋል፤ ገና ወደ ዘርፉ ሊገቡ ውይይት ላይ የሚገኙ ወጣቶችን ልብ በስኬት ታሪክ በተስፋ ሞልተዋል።

ወጣቶች ወደስራ ፈጠራ ፕሮግራም በእምነት ሲገቡ ፋይዳው ስራ ከመፍጠር በእጅጉ የላቀ እና የተለቀ መሆኑን ተመልክተውታል። በከተማችን የተጀመረው የልማት እንቅስቃሴ ተጠናክሮ እንዲቀጥል፣ በስራ የማደግና የመለወጥ ባህላችን እንዲጎለብት፣ የወጣቱ የተደራጀ አቅም በአገር እድገት ላይ እንዲውል፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲፈቱና ሰላማችን በአስተማማኝ ሁኔታ ዘላቂ እንዲሆን የወጣቶችን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት አስፈላጊነቱን የጋራ አድርገዋል።

አስተዳደሩ የከተማዋን ወጣቶች በየወረዳው ሲያወያይ ተወያይቶ ለመበተን አይደለም። በየሴክተሩ፣ በየፈርጁ ልቅም ተደርገው ተጠንተው በእርግጥም ወጣቶችና ሴቶች ተጠቃሚ የሚያደርጉ የስራ አማራጮችን ይዞ በመቅረብም ነው። በኮንስትራክሽን ዘርፍ 39 ሺህ፣ በማኑፋክቸሪንግ እና በከተማ ግብርና 12 ሺህ 500፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአጠናቸው ልዩ ልዩ መስኮች 83 ሺህ 600፣ እንዲሁም በክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች 26 ሺህ በጥቅሉ ከ161 ሺህ በላይ ወጣቶችና ሴቶችን ቀጥታ ተጠቃሚ የሚያደርጉ የስራ እድሎች ቀርበዋል። የመስሪያና የመሸጫ ቦታ ዝግጅት፣ የሪቮልቪንግ ፈንድ እና የፋይናንስ ድጋፎችን አስተዳደሩ ዝግጁ በማድረግም ነው። ይህ ደግሞ የምግብ ዋስትና ፕሮግራምን ሳያካተተ ነው።

የስራ እድል አማራጮች፣ የመስሪያና የመሸጫ ቦታዎች፣ የፋይናንስ አቅርቦት እንዲሁም ከ60 ሺህ በላይ ወጣቶችና ሴቶች አጫጭር ስልጠና እንዲያገኙ የሚያስችል ዝግጅት የከተማ አስተዳደሩ ማድረጉ አስተዳደሩና መሪው ድርጅት ኢህአዴግ የመዲናችንን ወጣቶችና ሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ ምን ያህል ትጉ መሆናቸውን የሚያመላክትም ነው። በየወረዳው ተገኝተው የተወያዩ ወጣቶችም ተስፋ ሰንቀው፣ ሰርቶ መለወጥ ክቡርነቱን አምነው እዚያው ውይይቱ ቀጥለው አስር አስር ሆነው የተደራጁበት እውነታም የመንግስትና የወጣቱ መተማመን ተጨባጭ ምልክትም ነው።

ተስፋን ሰንቆ፣ እምነቱን አሳይቶ በየተደራጀበት የስልጠናና የእግር መትከል ተግባራት በቀጣይነት የሚካሄዱ ይሆናሉ። ይህን ተስፋ፣ ይህን አመኔታ በአግባቡ ተንከባክቦ የወጣቶችንና ሴቶችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ በየትኛውም ደረጃ ለሚገኝ አመራር የስኬት አይነተኛ መስፈርት ሆኖ እነሆ ቀርቧል። በየትኛውም ደረጃ የሚገኝ የድርጅት አባልና አመራር ለህዝብ የአለው ወገንተኝነት በሚታይ፣ ቆጥሮ በመቀበልና ቆጥሮ በማስረከብ አሰራር በሚፈፀም ተግባር የሚለካበት ዓይነተኛ አንገብጋቢ ተግባርም ሆኗል።

ስለዚህ በሁሉም የከተማዋ አደረጃጀትና እርከን ተስፋ ሰንቆ እምነት አሳድሮ ወደ ንቅናቄው የሚገባ ወጣት ሃይልን ስራውን መደጋፍና ማበረታት ይገባል። ወጣቶችና ሴቶች በስራ እድል ፈጠራ ጥረታቸው ላይ ለሚያጋጥማቸው ችግር የመፍትሄ አካል ሆኖ መገኘት እውነተኛ ኢህአዴግነት ነው። በራሳቸው በወጣቶቹ ዘንድ ሊንፀባረቅ የሚችልን በስራ ባህል ላይ የአመለካከት መጓደል ተከታታይነት ባለው ግንባታ ማስተካከል፣ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትንና ተግባርን ወጣቶቹ ራሳቸው በፅናት እንዲታገሉ ማድረግም የማይታለፍ የልማታዊ ዴሞክራሲያዊነት መለያም ነው።

ህዳሴ ጋዜጣ ርእሰ አንቀፅ

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*